ፀጋ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን

 




የህይወት መና


“ ወደ ጉብኝቱ እንግባ ”


ባለፈው እትማችን እንዳየነው በእግሩ ስር በአውድማው ላይ ያደረችው ሩት በውስጧ የተቀመጠ ጥያቄና መሻት ይዛ ነበርና፤ ሲነቃ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በኔ ላይ ጣል አለችው። ከገረዶችህ ጋር በቃርሚያ መዞር ሰልችቶኛል የማይሞላ የማያሳርፍ ህይወት ነውና ዛሬ በእግርህ ስር መሆንን የመረጥኩት ህይወቴንና ታሪኬን መለወጥ ስለፈለኩ ነው። መቼውንም ቢሆን በዘመናቸው የእግዚአብሄርን ክንድ የተለማመዱት ሰዎች በእግሩ ስር መሆንን ያወቁበት ብቻ እንደሆኑ መጽሃፍ ቅዱሳችን አበክሮ ያስተምረናል። በቃርሚያ ዞራ ያልሞላላትንና ወደ ግቧ ልትመጣበት ያልቻለችው ሩት በእግሩ ስር መሆንን ስትመርጥና በእግሩ ስር ስታድር በታሪዃ ላይ በህይወቷ ላይ ታላቅ ነገር ተከሰተ። “ አሁንም ልጄ ሆይ አትፍሪ የምትጠይቂውን ሁሉ አደርግልሻለሁ አንቺ ምግባረ መልካም ሴት መሆንሽንም የሃገሬ ሰው ሁሉ ያውቃልና። ” ለሩት በእግሩ ስር ላደረችው የዋርሳዊ መልስ የምትጠይቂውን የምትሺውን ሁሉ አደርግልሻለሁ የሚል ነበር። የዚህች ሴት ጥያቄ ዋርሳዬ ሁን ወይንም ዋጀኝ የአንተ አድርገኝ ከአንተ በቀር እኔ ለማንም መሆን አይገባኝም በእግርህ ስር ያለሁት ራሴን ለአንተ ለመስጠት ፈጽሞ በአንተ ውስጥ ለመኖር ነው አለች። ቦዔዝም አለበሳት በእግሩ ስር ሌሊቱ እስኪያልፍ እንድትቆይ አደረጋት። እስቲ ዛሬ ከዚህ ሃሳብ በመነሳት በህይወታችን ምዕራፍ ላይ እግዚአብሄር ሊያመጣው ያሰበውን ታላቅ ነገር እያሰብን በጌታ ፊት በጸሎት እንበርታ። እንደቃርሚያ ገለባ የሞላበት ይህ የምንኖርበት አለም ጠዋትና ማታ ህይወታችንን አባክኖ አንዳች ሙላት ሳይሆነን ከብዙ ትርምስና ግፊያ ጋር እያመላለሰን ሳለ ከዚህ አድካሚና አሰልቺ የቃርሚያ ህይወት ዘወር ብለን ዋርሳችን በሆነው በጌታ እግር ስር ለመሆን ብንወስን በላያችን ሊያልፍ ያለውን ሌሊት የጸጋውን ልብስ ለብሰን በአውድማው ላይ ከውዳችን ጋር ሌሊቱን እናሳልፍ። “ እኔ እቤዥሻለሁ ” የሩት ናፍቆት የነበረው ቤዛ የሚሆናትን መፈለግ ነበር። ከጊዜያዊ ነገር ውስጥ ራሷን አውጥታ ዘላለማዊ በሆነው ነገር ውስጥ ለመጨመር ነበር ናፍቆቷ፤ ስለዚህ ጥያቄዋ የመቤዠት ስለነበር እርሱም እኔ እቤዥሻለሁ፣ አድንሻለሁ፣ የራሴ አደርግሻለሁ፣ ገንዘቤ ትሆኛለሽ የሚል ዋስትና ያለው የሚያስተማምን የህይወት ቃል ተቀበለች። ሩት የወደፊቷን ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን የተቀበለችው የለበሰችውን መደረቢያ አስወልቆ ስድስት መስፈሪያ ገብስ ወደ ጎተራ የሚገባውን፣ ገለባ የሌለበትን የጠራውን አሸከማት። ጌታ በእግሩ ስር ላሉት የፍጻሜያቸው ዋስትና ብቻ ሳይሆን የሚሆነውን ለአሁን ወቅት ላሉበት የኑሮና የህይወት ጥያቄ በበረከቱ መልስ አለው። በእግሩ ስር ያደረችዋ ሩት ከቃርሚያ ተገላግላ ውዷ ዋርሳ ሆኗት በእርሱ ተዋጅታ ለእርሷና ለአሮጊቷ የኑሮ መልስ በረከት ተቀበለች። በዚህ አላበቃም ሲነጋ በአደባባይ የእርሱ የሆነችለት ዋርሳዋ ስለ እርሷ መስክሮ ወደ ህይወቷ ፍጻሜ በድንቅ አስገባት። የሚኖሩበት አለም የህይወት ውጣ ውረድ ግራ መጋባት ብቻ ሳይሆን ላሉበት ህይወት መልስ ካሳጣዎት የነገሮች መፍቻ ያለው ጌታ የእርሶን ውሳኔ ይፈልጋልና ዛሬ ካሉበት ነገር ውልቅ ብለው በመውጣት የክብሩ ጌታ ወዳለበት ወደ ክብሩ ዙፋን ፊት በመምጣት ከአሁኑ አለም የሚዋጁበትንና ለኑሮ ትርጉም ጣዕም የሚያገቡበትን የመንፈስ ቅዱስን ሃይል ተቀበሉ። እግዚ/ን የሚፈልጉ ሁሉ ከመልካም ነገር አይጎድሉምና።

አብረን እንትጋ
በጌታ ፍቅር
ፓስተር ሃብቴ አዳነ